
የቫይታሚን ዲ እጥረት እጅግ በርካታ ሰዎች ላይ ይከሰታል።ጥናቶች እንደሚያሳዩት የቫይታሚን ዲ እጥረት 50% የሚሆነውን የአለም ህዝብ ያጠቃል።በተለይም ደግሞ ጥቁር ሰዎች ላይ በብዛት ይከሰታል ። ይህም የሆነው ጥቁር ቆዳ ከፍተኛ የሜላኒን (melanin) መጠን ስላለውና የፀሐይ ብርሃንን ወደ ውስጥ ስለማያሳልፍ ነው።
ጥናቶች እንደሚያሳዩት ከሆነ ቫይታሚን ዲ እጥረት በቀጥታ ስንፈተ -ወሲብን ያመጣል( Cause and effect ) ባይባልም ተጋላጭነትን ግን ይጨምራል ወይንም ደግሞ ቫይታሚን ዲ እጥረት እና ስንፈተ -ወሲብ ተያያዥነት እንዳላቸው ያሳያሉ። ይህም ማለት አነስተኛ ቫይታሚን ዲ መጠን በደማቸው ውስጥ ያላቸው ሰዎች ለስንፈተ – ወሲብ ተጋላጭ የመሆን ዕድላቸው ከፍተኛ ነው ማለት ነው።
ይህም ብቻ አይደለም አነስተኛ የቫይታሚን ዲ መጠን በደማቸው ውስጥ ያላቸው ሰዎች ለፕሮስቴት ካንሰር ተጋላጭ እንደሆኑም ጥናቶች አመላክተዋል።
በተለይም የደም ውስጥ የቫይታሚን ዲ መጠን ከ20 ng/ml በታች ከሆነ ተጋላጭነቱን በከፍተኛ መጠን ይጨምራል። እጅግ አነስተኛ የቫይታሚን ዲ መጠን ያለው ሰዉ የስንፈት ወሲብ ችግር ካጋጠመው ፣ የቫይታሚን ዲውን መጠን ብቻ በማስተካከል ያለምንም ተጨማሪ መድሀኒት መፈወስ ይችላል ማለት ነው ። ስለሆነም የቫይታሚን ዲን መጠን በላብራቶሪ ምርመራ ማወቅ በጣም አስፈላጊ ነው።
ቫይታሚን ዲን ከሶስት አይነት ነገሮች ማግኘት ይቻላል። ከፀሃይ ብርሃን ፤ ከምግብ እንዲሁም ከመድሃኒት (nutritional supplement) ማግኘት ይቻላል።
በቫይታሚን ዲ የበለፀጉ ምግቦች የሚከተሉት ናቸው። ስብ ያላቸው ዓሣዎች ለምሳሌ salmon fish, tuna , Sardin ፤ እንቁላል ፤ እንጉዳይ (mushroom) እንዲሁም የበሬ ጉበት ናቸው።
በሃኪም የሚታዘዙ በመርፌ ና በሚዋጥ (tablet ) የሚሰጡ መድሃኒቶችም ሲኖሩ እነዚህ በአጭር ጊዜ ውስጥ የቫይታሚን ዲ መጠንን ለማስተካከል ያግዛሉ።
በአጠቃላይ አነስተኛ የ ቫይታሚን ዲ መጠንን በምርመራ በማወቅ እና ተገቢውን ህክምና በመውሰድ የወሲብ ህይወትን ማሻሻል ይቻላል።