የዘር ፍሬ አካባቢ እብጠት በተለያዩ ምክንያቶች ሊከሰት ይችላል ከነዚህም መካከል የሚከተሉት ዋናዋናዎቹ ናቸው
1) የዘር ፍሬ ዙሪያ ፈሳሽ መከማቸት /HYDROCELE
የዚህ ችግር መንስኤ ብዙ ጊዜ ባይታወቅም አልፎ አልፎ ግን ከአባላዘር በሽታ ጋር ተያይዞ ይከሰታል ።
ህክምናውም ቀላል ቀዶ ህክምና ሲሆን በዘር ፍሬ ዙሪያ የተከማቸውን ፈሳሽ በማፍሰስ መልሶ እንዳይከማች ማድረግ ነው ።
2)በዘር ፍሬ አካባቢ የሚገኙ የደም ስሮች ማበጥ/VARICOCELE
በዘር ፍሬ አካባቢ የሚገኙ የደም ስሮች(veins) ማበጥ ከ ቀላል የዘር ፍሬ አካባቢ ህመም ባሻገር ለወንዶች የመካንነት ችግር ያጋልጣል ።
3)የዘር ፍሬ ካንሰር/ TESTICULAR TUMOR
የዘር ፍሬ ካንሰር ብዙ ጊዜ እድሜያቸው ከ15-35 ውስጥ በሚገኙ ወጣት ወንዶች ላይ ይከሰታል ።
የዚህ ካንሰር ዋናው ምልክት ህመም የሌለው እብጠት ነው/ painless testicular swelling ነው::
ይህ ካንሰር ሳይሠራጭ ቶሎ ከተገኘ ውጤታማ የሆነ ህክምና ሲኖረው ፤ ነገር ግን ብዙ ጊዜ ከዘር ፍሬ እብጠት ባሻገር ህመም ስለማይፈጥር ሰዎች ወደ ህክምና ተቋም የሚመጡት በጣም ዘግይተው ነው ። ይህም ህክምናውን ከባድ ያደርገዋል።
4)የዘር ፍሬ መታጠፍ/ TESTICULAR TORSION
ይህ ችግር እጅግ በጣም ድንገተኛና አጣዳፊ ከመሆኑም ባሻገር ከፍተኛ የሆነ ህመም አለዉ። ይህ ችግር ቡዙ ጊዜ በታዳጊ ወጣቶች ላይ ይከሰታል ።ይህ ችግር የሚስተካከለው በአስቸኳይ ቀዶ ህክምና ሲሆን በስድስት ሰአታት ውስጥ ካልተስተካከለ ወደ ዘር ፍሬ የሚሄደው ደም ስለሚቋረጥ ለመካነነት ችግር ይዳርጋል ።
5) የዘር ፍሬ እና አካባቢው ኢንፌክሽን/EPIDIDYMO-ORCHITIS
ይህ ችግር በአብዛኛው ከአባላዘር በሽታ ወይም ከሽንት ቧንቧ ኢንፌክሽን ጋር የተያያዘ ሲሆን ባክቴሪያዎች ከሽንት ቧንቧ ወደ ዘር ፍሬ በማለፍ ኢንፌክሽን ወይም መቆጣት ሲፈጥሩ የሚከሰት ችግር ነው ። ምልክቶቹም ከፍተኛ የሆነ የዘር ፍሬ አካባቢ ህመም ፣ትኩሳት ፣ ሲሸኑ ማቃጠል እንዲሁም ከብልት የሚወጣ ፈሳሽ ተጠቃሽ ናቸው ።
6) የልብ ድካም ፣ የኩላሊት እንዲሁም የጉበት ችግሮች
እነዚህ በሽታዎች በተለያዩ የሰውነታችን ክፍል ፈሳሽ እንዲጠራቀም የሚያደርጉ ሲሆን ለምሳሌ እግር ላይ ፣ ፊት ላይ እንዲሁም አንዳንዴ የዘር ፍሬ አካባቢ ላይ ፈሳሽ እንዲጠራቀም በማድረግ ሊያሳብጡት ይችላሉ።
በአጠቃላይ የዘር ፍሬ እብጠት ከቀላል እስከ ከባድ በሆኑ ችግሮች ምክንያት ሊከሰት ይችላል ። እንደ ጥሩ አጋጣሚ ሆኖ ለአብዛኛው የዘር ፍሬ እብጠት ችግሮች ውጤታማ የሆነ የህክምና አማራጭ ስላላቸው እንደዚህ አይነት ችግር ካጋጠምዎት ወደ ጤና ተቋም በመምጣት ምርመራና ህክምና ማድረግ ያስፈልጋል ።
ከዚህ በተጨማሪ የዘር ፍሬ ካንሰር የመጀመሪያው ምልክት ህመም-አልባ የዘር ፍሬ ላይ እንደ ጠጠር ያለ እብጠት ሲሆን ፣ ችግሩ ሳይባባስ ቀድሞ ለማወቅ በየጊዜው የዘር ፍሬዎት ላይ እብጠት መኖር አለመኖሩን ቼክ ማድረግ ያስፈልጋል ።